ዓባይ ከግብጽ ይልቅ ለኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ምርጫ ነው“ አቶ ታደሰ ጥላሁን የኢትዮጵያ ነዳጅ ኩባንያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት

 

አዲስ አበባ፡- ግብጽ 96 በመቶ የሃይል ምንጭ የምታገኘው ከተፈጥሮ ጋዝና ከነዳጅ ሲሆን በአንፃሩ ኢትዮጵያ 88 በመቶ የሃይል ምንጯ ደንን በመመጠር በመሆኑና ይህ ደግሞ በርሃማነትን ስለሚያስፋፋ ከግብጽ ይልቅ ለኢትዮጵያ ዓባይ የመኖርና ያለመኖር ምርጫ መሆኑን የኢትዮጵያ ነዳጅ ኩባንያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ገለፁ፡፡
የማህበሩ ፕሬዚዳንትና የኖክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የግብጽ ዋነኛ የሃይል ምንጯ በዓባይ ወንዝ ግድብ ሠርታ የምታመነጨው ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋዝ (51 በመቶ)፣ ከነዳጅ (45 በመቶ)፣ ቀሪውን ከድንጋይ ከሰልና ከሌሎች የሃይል ምንጮች የምታገኘው ነው፡፡ በአንፃሩ 88 በመቶ ኢትዮጵያ ታዳሽ የሃይል ምንጭ ከእንጨትና ከእንስሳት ዕዳሪ (ባዮ ማስ) የሚገኝ በመሆኑ አሁንም አብዛኛው ህዝባችንና እናቶቻቸን ምግብ ለማብሰል ጫካን እየመነጠሩ ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ደግሞ በአገራችን ድርቅን በማስፋፋት ከድህነት እንዳንወጣ ያደርገናል ብለዋል፡፡
ግብጽ ከውሃ የሚገኝ ሃይል በወሳኝነት የማያስፈልጋት መሆኑን ከሃይል አማራጭ ምንጮቿ መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ታደሰ፤ ኢትዮጵያ ግን የሃይል ፍላጎቷን ከውሃ ማግኘት ካልቻላች ድህነትን ለማሸነፍ የያዘችው ግብግብ በፍፁም ሊሳካላት አይችልም ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው የህዳሴ ግድብ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ሃይል ለኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ ሃይል ምንጭ ከመሆኑ ጎን ለጎን እናቶቻችንም ሆኑ እህቶቻችን ከአካባቢያቸው እርቀው ዛፍ እየቆረጡና ደን እየመነጠሩ የሚጠቀሙበትን ሁኔታ ያስቀራል፣ ግብርናውንም ለማዘመን ያግዛል ብለዋል፡፡
ግብጽ ለህዝቦቿ መቶ በመቶ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ያሳካች መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታደሰ፣ በአንፃሩ
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ገና 44 በመቶ ገደማ መሆናችንን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የእርሻ ኢኮኖሚና የሃይል ምንጭ ወደ ዘመናዊነት ካልተቀየረ የዓባይ ወንዝም ሆነ የተፋሰሶቹ ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ገልፀው የኢትዮጵያ የውሃ ምንጭ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲመነጭ ዓባይም የሦስቱ አገራት ህዝቦች በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ጠቀሜታ እንዲውል በኢትዮጵያ ተራራና ሸንተረር የአካባቢ ጥበቃ ላይ ግብጽና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ሆነው
ማልማትና መደገፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ግብጽ የዓባይ ውሃን ለመጠጥና ለመስኖ ልማት ብቸኛው አማራጫችን ነው የሚሉት ትርክት ሀሰት መሆኑን አውስተው ግብጽ ለአንድ ሺህ ዓመታት በላይ የሚያገለግላት ከፍተኛ የከርሰ ምድር ክምችት ያላት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ታደሰ ገለፃ፤ ዓባይ ብቸኛው ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ አይደለም፡፡ በዓለማችን 286 የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ በአፍሪካ 63፣ በሰሜን
አሜሪካ 19፣ በደቡብ አሜሪካ 65፣ በእስያ 73፣ በአውሮፓ 66 ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል በአፍሪካ የሴኔጋል ተፋሰስ ከጊኒ አንስቶ ማሊን ሞሪታኒያንና ሴኔጋልን አቋርጦ አትላቲክ ውቂያኖስ የሚገባ ነው፡፡ ይህም በሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በትብብር እየለማ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ሴኔጋል አንድ ማሊ አራት፣ ሞሪታኒያ ሁለት ጊኒ ሦስት ግድቦችን ገንብተውበታል፡፡
በዓለም ላይ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የተፋሰሱ አገሮች በስምምነት የሚያለሙበት ሁኔታ መኖሩን አውስተው ግብጽ አምስት ግድቦችን በዓባይ ላይ ሠርታ በእጅጉ እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡ በአንፃሩ የዓባይ ወንዝ መነሻና ወንዙን አመንጪ የሆነችው ኢትዮጵያ አንድ ግድብ ዓባይ ላይ ስትገነባ ከመደገፍ ይልቅ መቃወሟ ጡት ነካሽ ያደርጋታል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ግብጾች የኢትዮጵያን ግድብ መቃወማቸው ለኢትዮጵያ ጥሩ ዕድል ነው፡፡ ምክንያቱም ይህንን ኢፍትሐዊ የሆነውን ድብቅ ሴራቸውን ለዓለም ህብረተሰብ ለመግለጽ አስችሏታልና ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ 2018 ባወጣው ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አለመሆን ዋነኛው የዕድገት እንቅፋት መሆኑን ለአገራት ምክረ ሀሳብ መስጠቱን አስታውሰው፤ ግብጾች በፈጠሩት የሀሰት ትርክት ምክንያት ባንኩ ለ92 አገሮች 500 በላይ ግድቦችን እንዲገነቡ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ሲሰጥ ባንኩ የህዳሴ ግድብን መደገፍ ባለመቻሉ በኢትዮጵያዊያን እናቶች ከመቀነታቸው በአበረከቱት አስተዋጽኦ እየተገነባ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“በመጪው ሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ሙሌት መጀመሩ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ደስታና ፍሬውን ለማጣጣም መቃረባችን ማሳያ ነው“ ሲሉ የተናሩት አቶ ታደሰ፤ በያዝነው የክረምት ወቅትም ሁሉም ዜጋ ችግኝ በመትክልና በመንከባከብ ለአገራችን ዘላቂ ልማትና ዕድገት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2012
ጌትነት ምህረቴ

 

 

Products and Services

 

 

Station Locator

Quick Contact

National Oil Ethiopia Plc
Airport Road Street
Addis Ababa, Ethiopia
Tel: +251116639494
Fax: +251116639495
P. O. Box: 951 code 1250
Email: info@noc.com.et

www.nocethiopia.com

Connect with us